ዓርብ፡ ዕለተ ስቅለት

Date:


በመ/ር ጌታቸው በቀለ
ዕለተ ዓርብ ለዓለም ቤዛ ሊኾን መድኃኔዓለም የተሰቀለባት፣ የሰው ልጆች በኃጢአት ቁራኝነት እንኖርበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመባትና ፍጹም ድኅነት ያገኘንባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበትን የምናስብበት ታላቅ ቀን ናት፡፡ /ማቴ.፳፯፥፴፭—፸፭/፡፡


ዕለተ ዓርብ ዓርብ የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ወይም ‹‹መልካም ዓርብ›› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በ30 ብር ለመሸጥ ከአይሁድ ጋር አምላኩን አሳልፎ ለመስጠት በተስማማው መሠረት አሳልፎ ሰጣቸው። ሐሙስ ማታ ተይዞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት፣ ሊቃውንትና የሕዝቡ ሽማግሌዎች በሸንጎአቸው ተሰብስበው ሌሊቱን ሙሉ ሲከሱትና ሲወቅሱት ካደሩ በኋላ በመጨረሻ በመስቀል ስቅላት እንዲቀጣ የራሳቸውን ፍርድ ሰጥተው ለፍርድ አፈጻጸም ወደ ሮማዊው ገዢ ወደ ጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ወንጀለኛ አለመኾኑን ቢያረጋግጥም ከሳሾቹን ለማስደሰትና ምድራዊ ሥልጣኑን ለማቆየት ሲል እንዲሰቀል ተወሰነ።

በኋላም ከጲላጦስ ተቀብለው ከግንድ አስረው ጭፍሮቹ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር 6666 ጊዜ ገርፈውታል። የተለያዩ መከራዎችን ሲያጸኑበት ከቆዩ በኋላ ስድስት ስዓት ሲኾን ቀይ ግምጃ አልብሰው ግራ ቀኝ ፊት ኋላ ኾነው እያዳፉ ወስደው በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ሰቀሉት። ትንቢት “ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር” ተብሎ ትንቢት ተነግሯልና። /መዝ.፸፫፥፲፪/፡፡

ሰባቱ አጽርሐ መስቀል

ይህ ዕለት ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል (የፍቅር ቃላት) የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ እነዚህም ቃላት በየራሳቸው ጥልቅ ምስጢር ያላቸው ሲሆኑ የማዳኑ ሥራም የሚገልጹ ናቸው፡፡
✍️ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” /ማቴ.፳፯፥፵፮/
✍️ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” /ሉቃ.፳፫፥፴፬/
✍️ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” /ሉቃ.፳፫፥፵፫/
✍️ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” /ሉቃ.፳፫፥፵፮/
✍️ “እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ” /ዮሐ.፲፱፥፳፮/
✍️ “ተጠማሁ” /ዮሐ.፲፱፥፳፷/
✍️ “ተፈጸመ” /ዮሐ.፲፱፥፴/

እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ለየ፡፡ በስቅለት ዕለት እነዚህ በንባብና በዜማ እያልን እንሰግድለታለን፡፡
የስቅለት ተአምራት

ጌታችን በዕለተ ዓርብ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለጽ ተአምራት አሉ፡፡ እነዚህም፡- በሰማይ ሦስት ተአምራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚህም የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መልበስ፣ የክዋክብት መርገፍ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በመስቀል ላይ ያለውን የአምላካቸውን እርቃን ላለማሳየት ነው፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ይህንን “ፀሐይ ፀልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወክዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ አይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ” ሲል ገልጾታል፡፡ እንዲሁም በምድር አራት ተአምራት ታይተዋል፡፡ እነዚህም የቤተ መቅደስ መጋረጃ መቀደድ፣ የዐለቶች መሰንጠቅ፣ የመቃብሮች መከፈት፣ የሙታን በአጸደ ሥጋ መነሣት ናቸው /ማቴ.፳፯፥፶፬/፡፡

እነዚህ ተአምራት በመስቀል ላይ የተሰቀለው ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ለሰው ልጆች ያረጋገጡ ምልክቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ተአምራት አይተው በጌታችን ያመኑ ነበሩ፡፡
ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

ዕለተ ዓርብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መተላለፋችን የቆሰለበት፣ ስለ በደላችንም የደቀቀበት፣ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መስዋዕት ያደረገበት፤ በእርሱም ቁስል እኛ የተፈወስንበት፤ በሞቱም የሞት ስልጣን የተሻረበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ዐሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት፣ እኛም እነዚህን እያሰብን የምንሰግድበት፣ በተደረገልን ቤዛነት እየተደነቅን ፍቅራችንን አምልኮታችንን የምንገልጥበት ዕለት ነው፡፡


ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ አንድ ሁለት ብሎ በቁጥር ማስቀመጥ ከባድ ቢኾንም በቤተክርስቲያናችን 13 ሕማማተ መስቀል እየተባሉ የሚጠሩ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተቀበላቸው መከራዎች አሉ። እነዚህም በተለያዩ መምህራን በተለያዬ መንገድ ስለሚቆጠሩ በዚህ ጽሑፍ በሚከተለው መልኩ ቀርበዋል።

13ቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት፡ ሁለት እጆቹን የፊጥኝ ወደ ኋላ መታሰሩ፣ ምራቃቸውን ተፉበት፣ ፊቱን በጥፊ መመታት፣ ጀርባውን በጅራፍ መገረፉ፣ ራስን በዘንግ መመታት፣ልብሱን ተራቆተ፣ የሾህ አክሊል መድፋት፣ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ ሮዳስና አዴራ በተባሉት ችንካሮች መቸንከር)፣ እና መራራ ሐሞትን መጠጣቱ ናቸው፡፡ በስቅለት ዕለት ለእኛ ሲል እነዚህን ሕማማተ መስቀል መቀበሉን እያሰብን የአምልኮ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡
ዕርቀ ሰላም የተገኘበት

ዕለተ ዓርብ ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) የታረቁበት፤ የተስማሙበት ዕለት ነው፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው /ኤፌ. ፪፥፲፤ ቆላ.፩፥፳/፡፡ የስቅለት ቀን የገነት በር የተከፈተበት በአንጻሩ ደግሞ ሲኦል የተበረበረበችበት ነው፡፡

በአዳም በደል ምክንያት አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችው ገነት የተከፈተችበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሠልጥና የነበረችው ሲኦል የተበረበረችበት፣ ነፍሳት ከሲኦል ወጥተው ወደ ገነት የገቡበት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ጥልን በመስቀሉ ገደለ” ሲል የገለጸው /ኤፌ.፪፥፲፮/ በእነዚህ መካከል የነበረው ጥል ማብቃቱንና ፍጹም ሰላም መስፈኑን ያሳያል፡፡


የመስቀል ስጦታዎች

በዕለተ ዓርብ ታላላቅ ስጦታዎችን አግኝተናል፡፡ እነዚህም፡- የምንጠመቅበት ማየ ገቦ፣ የምንድንበት ሥጋውና ደሙን እንዲሁም የምታማልድ እናት የተሰጠንበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ዓርብ ተጠምቀን ድኅነት የምናገኝበት ውኃ ከጎኑ የፈሰሰበት፣ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ያገኘንበት ዕለት ነው/ዮሐ. ፲፱፥፴፬/፡፡

“ስለ ዓለም የሚቆረሰው ሥጋዬ የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው” እንዲል /ማቴ ፳፯፥፳፯/፤ ቤተክርስቲያንም የተዋጀችው በዚሁ በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ ሥጋውንና ደሙን በመስቀሉ ላይ አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ሥር ድንግል ማርያም በዮሐንስ አማካኝነት እናት እንድትሆነን፣ እኛም ልጅ እንድንሆን የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ እናቱ እናት እንድትሆነን በይፋ የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ “እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ” /ዮሐ. ፲፱፥፴፮/ ብሎ ርኅርኅት እናት ከመሰቀል ሥር በዕለተ ዓርብ ሰጠን፡፡

የሰው ልጅ ድኅነት ያገኘበት

የስቅለት ዓርብ የሰው ልጅ ከዲያብሎስ እሥራት የተፈታበት ዕለት ነው፡፡ የሰው ልጆች በቁራኝነት ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ የስቅለት ዓርብ የሲኦል አበጋዝ ዲያብሎስ በንፋስ አውታር የታሠረበትና ሥልጣኑ የተሻረበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ታስሮ የነበረው አዳም የተፈታበትና ወደ ገነት የተመለሰባት ናት፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲፈረድበት ወንጀለኛ የነበረው በርባን ተፈታ፡፡ ጌታችን በሥጋው ሲሞት ደግሞ አዳምና ልጆቹ በሙሉ ተፈቱ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ “በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ፤ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ፤ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ፤ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” እንዳለ፡፡ እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ነው እርሱም ደግሞ ሄደ በሲዖል ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው” /፩ጴጥ.፫፥፲፰/ እንዳለው ጌታችን በሲኦል እስራት የነበሩትን ነፍሳት ነጻ አወጣቸው፡፡


የስቅለት ዓርብ ስያሜዎች


ዕለተ ዓርብ ድኅነት የተፈጸመባት ልዩ ቀን ናት፡፡ በዚህች ዕለት በየሰዓቱ የተለያየ ምስጢራት ተፈጽመውባታል፡፡ ይህች ዕለት በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ምስጢራዊ ስያሜዎች አሏት፡፡ የስቅለት ዓርብ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የኾነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ኾኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ እንደ ብራና ተወጥሮ መዋሉን ለማስታወስ የስቅለት ዓርብ ተብሏል “ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ፣ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር” እንዲል /ማቴ.፳፯፥፴፭/፡፡

መልካሙ ዓርብ

ከጌታ በፊት መስቀል ወንጀለኛ የመቅጫ መሣሪያ ነበር፡፡ ሰውን ሰቅሎ መግደል የተጀመረው በፋርስ ነው፡፡ በፋርስ ሰዎች አምልኮት የመሬት አምላክ(Ormuzd) ይባላል፡፡ ወንጀለኛ በሀገራቸው ሲገኝ ቅጣቱን በመሬት የተቀበለ እንደኾነ አምላካቸው እንዳይረክስ ወንጀለኛውን ሁሉ በመስቀል ይስቅሉት ነበር፡፡ ይህ አድራጎት እንደ ልማድ ኾኖ በሮማ ግዛት ሁሉ የተለመደ ሕግ ኾነ፡፡

(ORTHODOXY- A creed for today, plain talks on the orthodox faith based on the Nicene Creed, ANTHONYM. CONIARIS) 1972, p.128፡፡ በኦሪትም ሥርዐት በመስቀል በስቅላት የሚቀጡ ሁሉ ርጉማን ውጉዛን ነበሩ፡፡ ከጌታ በኋላ ግን የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምሕረት ምልክት፣ የሕይወት ዓርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ፣ የነጻነታችን ዐዋጅ የተነገረበት ኾነ፡፡ በሞቱ ሕይወትን ስለ አገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

እንደ ማጠቃለያ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /፩ኛ ቆሮ.፩፥፲፷/፡፡ እንዲል ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል፣ ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.፳፯፥፴፭-፸፭/፡፡

በአጠቃላይ የስቅለት ዓርብ ጌታችን በቤተልሔም የተጀመረው የሰውን ልጅ የማዳኑ ሥራ የተጠናቀቀበት፣ ጌታም ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ የሠራበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ዓርብ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የተባለው የተፈጸመበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በመስቀል ላይ “ተፈጸመ” ያለው፡፡

ኦርቶዶክሳውያንም በዚህ ዕለት ጌታችን ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ እያሰብን፣ ስለ ኃጢአታችንም እያለቀስን፣ ስለ ማዳኑም ሥራ ምስጋናን እያቀረብን ስንሰግድ እንውላለን፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን “አቤቱ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበን” እያልን እንማፀናለን፡፡ በጾማችንን ፍጻሜ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል እመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ሃይማኖት አበው
✍️ መጽሐፈ ቅዳሴ
✍️ ከቅስለት እስከ ትንሣኤ
✍️ The Nicene Creed, ANTHONYM. CONIARIS
✍️ Encylopedia of Aethiopica

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...