በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታየው ወታደራዊ ውጥረት ከቀጥታ የጦርነት ቀጠናው ባለፈ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ላይ የገንዘብና የእንቅስቃሴ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፣ በኢራን፣ እስራኤልና አሜሪካ መካከል ያለው ግጭት ተቋሙን በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እያስከተለበት ነው።
ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት አየር መንገዱ ወደ ቀጠናው ቁልፍ ከተሞች ማለትም ወደ ዱባይና እስራኤል በቀን ሦስት ጊዜ፣ ወደ አማን ደግሞ ሁለት ጊዜ በረራዎችን ያደርግ ነበር።
ሆኖም የሰማይ ላይ ደህንነት ስጋት በመጨመሩ፣ ተቋሙ በቀን በአማካኝ 15 በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል። ይህም በሳምንት ሲሰላ ከ101 በላይ የመንገደኞች በረራዎች ከአየር ጠባይ ውጪ በሆነ ምክንያት እንዲቀሩ አድርጓል።
በድምሩ በሳምንት ከ45 እስከ 50 ሺሕ መንገደኞችን የማጓጓዝ አቅም የነበረው አየር መንገዱ፣ አሁን ላይ የጭነት በረራዎችን ጨምሮ በሳምንት 160 የሚደርሱ በረራዎች ላይ እገዳ ለማድረግ ተገዷል።
