የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው የሁለት ወራት ግምገማ ጎዶሎ ነው!

Date:

መንግሥት ከሁለት ወራተ በፊት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ የማሻሻያው ዓላማ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን በማበረታታት ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ብሎም የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ የመንግሥትን ዐቅም ማሳደግ ነው ተብሎ ተገልጾ ነበር።

በተጨማሪም ፕሮግራሙ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለትን መፍታት፣ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፣ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶትን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል በመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ማጠናከርና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ቁልፍ ዓላማና ግቦቹ መሆኑም ተጠቅሶ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ፕሮግራሙ ከተገበረበት ጊዜ ትክክለኛነት አኳያ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ መንግሥት የውጪ ምንዛሪን በበቂ ሁኔታ በማግኘት የልማት ውጥኖቹን እንዲያሳካበት ሊረዳው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ኾኖም ግን እንዲህ ካለው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ የከፋ መኾኑን መናገር ይቻላል፡፡ ቀዳሚው ምክንያት ደግሞ፣ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በየደረጃው መደረግ ሲኖርበት በአንዴ የተደረገው ማሻሻያው የዋጋ ግሽበትን የሚያባብስ መኾኑ ሲኾን፣ በሁለተኛነት ደግሞ አሁን ባለው የግጭት ሁኔታ የታለመውን የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማሻሻል እና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ጥያቄ የሚጭር በመሆኑ በታለመለት ደረጃ መሄዱ አጠራጣሪ ስለሚኾን ነው፡፡

ከሰሞኑን ደግሞ አይኤምኤፍ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በፖሊሲ ትግበራው የሁለት ወራት አፈጻጸም ዙርያ በየፊናቸው ሪፖርቶችን አውጥተዋል፡፡ ሪፖርቶቻቸ ላይ ግን በተገቢው መልጁ ያልተዳሰሱና ቀጣዩን ግዜ የከበደ የሚያደርጉ ጉዳዮች በተገቢው አለመነሳታቸው መጪውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የኑሮ ውድነት ሁኔታ ከሚጠበቀውም በላይ አሳሳቢ እንዳያደርገው ግዮን ሥጋቷን ለመግለጽ ትወዳለች፡፡

የኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሬ ለውጥን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ስጋትን ፈጥሮ የነበረው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ እንደነበር ከማንም የተሰወረ አልነበረም፡፡ የአይ ኤም ኤፍ እና የመንግሥት ሪፖርቶች ደግሞ የዋጋ ግሽበት በተወሰኑ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከመስተዋሉ በቀር የተፈራውን ያህል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ኾኖም እንዲህ ያለው አደገኛ ድምዳሜ ጊዜያዊ ውጤት እንጂ ችግሩን በአግባቡ የቀረፈ ተደርጎ መገለጹ አሳማኝነት የለውም፡፡ ለአብነትም ከሰሞኑን መንግሥት የነዳጅን ዋጋ በየ3 ወሩ እንደሚከልስ አስታውቋል፡፡ የዚህ ሁነኛ ምክንያቱ መንግሥት በየሦስት ወሩ ከሚፈፅማቸው የነዳጅ ግዥዎች ጋር የሚያያዝ በመኾኑ ነው፡፡

በዚህም ሳቢያ ላለፉት ሁለት ወራት ሀገሪቷ እየተጠቀመች የነበረው ነዳጅ ቀደም ብላ ያስገባችውን ነዳጅ በመሆኑ ይህ ነው የሚል የነዳጅ ጭማሪ አለመደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፕሮግራሙ ‹‹የተፈራውን ግሽበት አላመጣም›› ብሎ ለመደምደም ማሣያ ሊኾን አይችልም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በቀጣይ የሚያስገባው ነዳጅ በተሻሻለው የምንዛሪ ተመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነዳጅ የመግዣ ዋጋ በእጅጉ እንደሚጨምር ስለሚጠበቅ ነው፡፡ ሌላው በመንግሥት በኩል የተገለፀው የዋጋ ግሽበት ከመቆጣጠር አንፃር በተወሰኑ ሴክተሮች ላይ ድጎማ ማድረግ አሁንም የሚቀጥል መኾኑ ነው፡፡ በተለይም የተለያየ ዐይነት ያላቸው የዘይት ምርቶችን ከውጭ ማስገባት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ባለፉት ሁለት ወራት ሲሰራ እንደቆየ ገልጿል፡፡ በነዚህ የሽግግር ግዜያት ውስጥ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ ምርቶች አንዱ ግን ዘይት መሆኑ አይካድም፡፡

ከዚህም ሌላ መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ የታክስ ስርዐቱን እየፈተሸ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ የታክስ አሰባሰብ አሰራር እንደሚከተል መግለጹን ከግንዛቤ ለሚከት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ዐቅምን ለማጠናከር በዋናነት የአገልግሎት ዋጋቸውን እንደሚጨምሩ መግለጻቸውንም አብሮ ለሚያሰናስል መጪው ግዜ ለኢትዮጵያ አኮኖሚና ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል እጅግ የከበደ እንደሚሆን ለመግለጽ ነብይ መኾን አይጠይቅም፡፡

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 217 ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...