የኢራን ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎች በአሜሪካ እና በእስራኤል በተደጋጋሚ በተፈፀሙ የአየር ድብደባዎች ምክንያት መዘጋታቸውን ኩባንያዎቹ አስታወቁ።
“የመጀመሪያ ግምታችን እነዚህን ክፍሎች እንደገና ማስጀመር ቢያንስ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንደሚወስድ ነው” ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢራን የሚገኘው የኩዜስታን የብረት ኩባንያ የኦፕሬሽን ምክትል ኃላፊ ሜህራን ፓክቢን ለኢራን መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የሞባራኬህ ብረት ኩባንያ በመሃል አገሪቱ የሚገኘው ማምረቻዎቹ “ከፍተኛ የሆነ ጥቃት በመፈጸሙ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል” ብሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቃቱ ባለፈው ሳምንት አርብ መፈጸሙን ዘግበዋል።
በፋብሪካዎቹ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በኢራን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ጨምረው ተናግረዋል።
ከዓለም ብረታ ብረት ማህበር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኢራን በዓለም አቀፍ ደረጃ 10ኛዋ ትልቋ የብረት አምራች አገር ነች።
ብረትን በአገር ውስጥ ለግንባታና ለማኑፋክቸሪንግ ከመጠቀም በተጨማሪ ወደተለያዩ የዓለም አገራት ትልካለች።
የፋብሪካዎቹ ምርት ማቆም ለዓመታት በተጣለው ማዕቀብ በተጎዳው የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የአቅርቦት ሰንሰለቶች እና ንግዶች ላይ ከፍተኛ አንድምታ ሊኖረው ይችላል።
ቢቢሲ የእስራኤልን የመከላከያ እና የአሜሪካን ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ስለ ጥቃቱ አስተያየት ጠይቋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “እስራኤል በኢራን ውስጥ ሁለት ትላልቅ የብረት ፋብሪካዎችን፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና የሲቪል የኒውክሌር ጣቢያዎችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መትታለች። እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመተባበር እርምጃ መውሰዷን ገልጻለች” ብለዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል የደህንነት ምንጭ ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ ጥቃቶቹ በኢራን ኢኮኖሚ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ጉዳት ያስከትላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የብረት ፋብሪካዎቹ ከኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል።
የአብዮታዊ ዘቡ ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ከአሜሪካ ጋር የተገናኙ የብረት እና የአሉሚኒየም ተቋማትን ዒላማ እንዳደረገ ተናግሯል።
ሐሙስ ዕለት የእስራኤል ጦር ከኢራን በርካታ ሚሳዔሎች መወንጨፋቸውን ሲገልጽ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ደግሞ ጦሯ ከኢራን የተተኮሱ 19 ሚሳዔሎችን እና 26 ድሮኖችን “አክሽፏል” ብላለች።
