በስፔን ባርሴሎና እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የሞባይል ዓለም አቀፍ ኮንግረስ ጎን ለጎን፣ ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ አቅሙን ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የሚያስችል ግዙፍ ስምምነት ከቻይናው ዜድ ቲ ኢ (ZTE) ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራርሟል፡፡
በዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ የተፈረመው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 647 አዳዲስ የኔትወርክ ጣቢያዎችን መገንባትን የሚያካትት ሲሆን፣ በዋናነትም ዘመናዊ የሞባይል ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የሀገሪቱን የ4ጂ የሕዝብ ሽፋን ወደ 95.5 በመቶ በማሳደግ የአገልግሎት ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽል ይጠበቃል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ከማፋጠኑ ባለፈ፣ የዲጂታል ሥነ-ምህዳሩን በማዘመን ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል።
ይህ ስምምነት ኩባንያው ከኤሪክሰን ጋር ካደረገው ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ አጋርነት ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ታምኖበታል።
