በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግዙፉ የችርቻሮና የጅምላ ንግድ ኩባንያ ከሆነው ካርፉር (Carrefour) ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያየ። ውይይቱ ካርፉር በኢትዮጵያ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ ላይ ሊሰማራ በሚችልበት ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዘለቀ ተመስገን፣ ለካርፉር ተወካዮች ኢትዮጵያ በቅርቡ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ስላደረገቻቸው አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎችና አማራጮች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
የካርፉር (Carrefour) አለም አቀፍ ፍራንቻይዝ ዳይሬክተር ኤማ ኮፔይ፤ የኢትዮጵያን ገበያ ለረጅም ጊዜ እንደ መዳረሻ ሲመለከቷት እንደነበር ገልጸው፣ የወጪና ገቢ ንግድ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኩባንያው ኮሜርሻል ዳይሬክተር ጄሮም ቦንዚ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሰማራት የሚያስችል የቢዝነስ ሞዴል እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አክለውም፣ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ቡድን በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ እንደሚልኩ ማስታወቃቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል።
እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም. በፈረንሳይ የተመሰረተው ካርፉር በአውሮፓ፣ እስያ፣ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ በሚገኙ ሱፐር ማርኬቶቹ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
