የአትሌቲክሱ ውይይት የወፍ በረር ትዝብቴ

Date:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት ቅዳሜ ከአትሌቲክስ አሰልጣኞች እና ባለሞያዎች ጋር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በሁለት አንኳር ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፤የአትሌቲክስ አሰልጣኞች መሰፈርት(Standard) እና በብሄራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞች ምርጫ መሰፈርት(Standard) ዙሪያ የከረሙ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።

ውይይቱን”…እኔ አትሌት ነበርኩ፤በጣም የማከብራቸው፣ሲያሠለጥኑኝ የነበሩ አሠልጣኞች ፊት በዚህ ደረጃ ቆሞ ለማውራት ትንሽ የፍርሃት ስሜት አለው የድሮውም አለቀቀኝም መሠለኝ እንግዲህ በዚህ ሂደት ብሳሳት ከወዲሁ ይቅርታ አድርጉልኝ”በማለት ከፍተኛ ትህትናና ክብር የተቀላቀለበት መልዕክት በማስተላለፍ የውይይቱን መጀመር በንግግሩ ያበሠረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን “የአሠልጣኞች መመዘኛ ለብዙ ዓመታት ሲንከባለል ቆይቶ ዛሬ ላይ ወደ ስራ አስገብተን፣ነገሮችን ተጋግዘን መስመር ወደምናሲዝበት አጀንዳ ወይም ዶክመንት ይቀርባል፤ዶክመንቱ የፀደቀ ነው፤የሚጎሉትን ወደፊት እያሟላን ለአትሌቲክሳችን መሠረት ያለው ነገር ለመጣል እንሞክራለን፣ እንሠራለን ብዬ አስባለሁ፤ይሄ መስፈርት የፀደቀ ነው ለማየት ሞክረናል ለምን እስከአሁን ችግሮች ገጠሙት?ለምን ወደስራ እስከአሁን ወደ ስራ መግባት አልተቻለም?የሚለውን ለማየትም ሞክረናል ግን ቀድመን አይተን በጊዜ እኛ ካልሞከርነው ለማስተካከል ስለምንቸገር ምንም እንኳን አንዳንድ ነገሮች የተስተካከሉ ባይሆኑም ወቅቱም ከዚህ የተሻለ ጊዜ ስለማይኖር ወደስራ ማስገባቱ ተገቢ ነው ብለን እናስባለን እሱ ላይ ሠፋ ያለ ውይይት እናደርጋለን” በማለት በአስተያየቱ በመቀጠል
“ውጤቶች ጥሩ ቢሆኑም መስመሩን ይዞ እየሄደ ነው ለማለት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፤እንዱ ማሳያ ይሄ ጥናት የብቃት ደረጃዎች እስከአሁን አለመተግበራቸው ነው፤”በካለ በኃላ ጥሪውን አክብረው የመጡትን በማመስገን ስብሠባው በይፋ መጀመሩን አብስሮ መድረኩን ጥናቱን ላቀረቡት ሙያተኞች አስረክቧል።

ዘግይቶ የጀመረውና ከቀኑ 8:00 እሰከ 1:00 የዘለቀው የውይይት መድረክን ሁሉንም በዚህ ፕላት ፎርም ለማቅረብ ገዳቢ ነገሮች በመኖራቸው፤ከዚህ በታች ባለው መልኩ አንኳር አንኳር ነጥቦችን በወፍ በረር ለመቃኘት ተሞክራል፤በቅድሚያ ከውይይቱ በጎ ጎን እንነሳ:-

      👉ከፍ ብሎ የታየው የውይይቱ በጎ ነገሮች

“በኮማንደር አትሌት ሰለሺ ስህን የሚመራው አዲሱ ስራ አስፈፃሚ በመድረኩ በርካታ አሠልጣኞች እንደተናገሩት ብዙዎች ለመድፈር የፈሩትንና ከተጠናና ከፀደቀ ዓመታት ያስቆጠረውን የብዙዎችን ቤት ማንኳኳት ብቻ ሳይሆን እስከማናጋት የሚያደርሠውንና መስመር በማስያዝ ሂደት ብዙዎችን ወደመስመር ውስጥ የማያስገባውና የሚያስወጣውን አጀንዳ ከተወረወረበት ሼልፍ ላይ አንስቶ አቧራውን አራግፎና ማሻሻያ አድርጎ ደፍሮ ለውይይት ማቅረቡ፣አዳምጦም ለማረም ሠፊ ልብ ይዞ መነሳቱ አድናቆት የሚያሠጠው ብቻ ሳይሆን ለለውጥ ቁርጠኛ መሆኑን ይጠቁማልና መልካም ጅማሮ በሚል ሊወደሱ ይገባል።

           👉ለሚዲያ ክፍት ማድረጋቸው

በስፖርቱ ምንም የሚደበቅ የለም በሚል አዲሱ አመራር ይሄንን ብዙ ፍላጎት ያለውን ትልቅ አጀንዳን የመንግስት የግል ሳይሉ ሳይከፋፍሉ ሚዲያ ላይ በር ሳይከረችሙ ክፍት በማድረጋቸው ያላቸውን በራስ መተማመን በግልፅ ያሳያል፤ሚዲያው በተሸራረፈና በግል ፍላጎት ላይ የተንተራሠ መረጃ በተሰባበረ መልኩ እንዳይደርሠውና የተሳሳተ መረጃ ወደ ህዝቡ እንዳይደርስ እንዲሁም በቂ ግንዛቤን እንዲያገኝ በማድረጉ በኩል ሚናው የላቀ ነውና በዚህ በኩል ወፈር ያለ ሙገሳ ይገባችኋል።

                 👉የውይይቱ ሰባራ ጎኖች

👉ለውይይት የተመረጠው ሠዓት የውይይቱን ጥልቀት ያላገናዘበ መሆኑ

ሲጀመር ይሄን ያክል ቢቆፈር የማያልቅ የሁሉንም ስሜት ዘቅዞ የመያዝ ትልቅ አጀንዳን ከዚህ ሁሉ ባለሙያ ጋር አደረኩ ለማለት ካልሆነ በስተቀር አይደለም በግማሽ ቀን በቀናት የሚጠናቀቅ እንዳልሆነ ለመናገር ልዩ ጠቢብ መሆንን አይጠይቅም፤ከዚህም በላይ አሠልጣኞች ስልጠና አላቸው በሚል ከስብሠባውና ከሚነሳው ሃሳብ ግዙፍነት አንፃር ሚጢጢ የሆነ ምክንያት ወደ ከሠዓት ተገፍቶ እሱም በሠዓቱ አለመጀመሩ የውይይቱን ጥልቀትና ስፋት ካለመረዳት ብቻ ሳይሆን ከመዘንጋት የመነጨ ክፍተት በመሆኑ መታረም አለበት።

👉የውይይቱ አጀንዳዎችና የኢንስትራክተር ሳሙኤል አድናቆት የተቸረው አቀራረብ

እንደተባለው ይሄ አጀንዳ ከ10 ዓመት በፊት ቢጠናም ከአራት ዓመት በፊት ታሽቶ ቢፀድቅም መሬት ማውረድ ሳይቻል አሁን ያለው አመራር ልቅ የሆነውን አሠራር ለማሠር የሄደበት ርቀት አሁንም የሚደነቅ ነው፤ጥናቱን በማቅረብ በኩል በሁለት ሠዎች የቀረበ ቢሆኑም ኢንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ የተፃፈውን በስድ ንባብ መልክ ያላቀረቡ፣ይልቁንም ተሰብሳቢው በቀላሉ እንዲረዳ የገፁበት መንገድ ከብዙዎች አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል።

ኢንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ ከመድረክ አያያዛቸው፣ከተክለ ሠውነታቸው፣ከአንደበታቸው በሚወጣው ቃል ፈትፍቶ የማጉረስ ያህል ቀለል አድርገው ለተሰብሳቢው ያቀረቡበት መንገድ ያላቸውን ዕምቅ አቅምና ጥልቅ ዕውቀት ያሳየ በመሆኑ ይሄን አለማድነቅ አይቻልም፤ለዚህ ማሳያው ደግሞ እሳቸው ባቀረቡት ላይ የተፈጠረ ጫጫታም፣ብዥታም አለመታየቱ አንደኛው ምስክርም ተደርጎ ሊወሠድ ይችላል።

                      👉የመድረክ አያያዝ

መድረኩን በዋናነት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ነበር ሲመራው የነበረው ማለት ይቻላል፤ ሠዎች ሃሳባቸውን ያለገደብ እንዲገልፁ የፈቀደበት መንገድ መልካም ቢሆንም (Time Limit) የሠዓት ገደብ አለመኖሩ የስብሠባውን መንፈስ ቀይሮታል ብቻ ሳይሆን ሃሳባቸውን መቋጨት የማይችሉና የሚደጋግሙ ከአጀንዳው ውጪ ለመምከር የሚሞክሩ ሠዎች መድረኩን እንደፈለጉ እንዲፈነጩበትና ውዱ ሠዓት እንዲባክን ሃሳብ ያላቸው እንዲሸፈኑ፣ከዚህ ከፍ ሲልም ለእኛ እንዴት ዕድሉ አይሠጠንም እንዴት ሌሎች ይናገሩናል የሚል ቁጣ ከማሠማት በዘለለ መድረክ ጥለው እስኪወጡ ያደረሠ ቀላል የማይባል ሚና ተጫውቷል፤የስለሺን በቀናነትና ለሠዎች ሃሳብ ክብር የመስጠት በክፋት ባይወሠድም ሃሳባቸውን በማይቋጩ፣በሚደጋግሙና አወራ ለመባል ብቻ በሚሽቀዳደሙ ሠዎች ምክንያት መድረኩን ቅርፅ ለማስያዝ ፈታኝ ሲሆንም ተስተውሏል።

    👉በስራ አስፈፃሚ ደረጃ በቂ ዝግጅት አለመደረግ

የተነሱትን ጥያቄዎች ኮማንደር ስለሺ ስህንና ኢንስትራክተር ሳሙኤል ለመመለስ ሲሞክሩ ታይቷል፤ከመድረክ ከሚወረወሩ ጥያቄዎችና ብዛት አንፃር በአንድና ሁለት ሠው ከሚመለስ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ዝግጅትና ክፍፍል ተደርጎ ምላሽ ቢሠጥበት ነገሮች ይበልጥ እንዲጠሩ የማገዝ አቅም ይኖረው ነበር፤ ከስድስት በላይ ስራ አስፈፃሚዎች ከመድረኩ መሪዎች ፊት ለፊት ተቀምጠው አንዳችም ቃል ሳይተነፍሱ፣ሃሳብ ሳይሠጡ መታየታቸው አንዳንዶቹ እንደውም ውይይቱ ሳያልቅ ምክንያቱ ይሄ ይሁን ሌላ ባይታወቅም ጥለው ሲወጡ፣ ቅሬታም ያሠሙበት ሁኔታ መታየቱና ከዚህ ከፍ ሲልም ለምን መጡ ስብሠባውን ለማጀብ?የሚል ስላቅንም እንደማስከተሉ እንደ ቡድን የስራ ክፍፍል ቢኖር ውይይቱንም ምላሹን የተሟላ ያደርገዋል የሚል ዕምነት አለ።

          👉ሙያተኞች ለምን ተጠሩ?

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌቲክስ አሰልጣኞች እና ባለሞያዎች ጋር ውይይት አደርጋለሁ ብሎ ነው የጠራው ነገር ግን በውይይቱም በጥናቱ ላይም አንድም ቦታ ስለሙያተኞች የተነሳ አንድም ነገር አለመታየቱ ለምን ተጠሩ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ከማስገደዱም በላይ በጥናቱ በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ አትሌቶች፣አሠልጣኞች ላይና ሚኒማ ላይ በማጠንጠኑ ፊዚዮቴራፒስቶችና የህክምና ባለሙያዎችም እነሱም በሚኒማ ነው እንዴ የሚመረጡት?የሚል ቀልድ የሚመስል ትልቅ መልዕክት ያለው ጥያቄ እንዲመዘዝ አድርጓል።አንዳንድ ሙያተኞችም የተጠራነው በማይመለከተን ነገር ነው ብለው እንዲወጡም ገፍቷቸዋል፤በአጭር ቃል ስብሠባውም ጥናቱም በሙያተኞች ዙሪያ ተጠርቶ ሙያተኞቹን ዘሏቸዋል፤ተገልለዋል፤ይሄም የስብሠባው ሌላኛው ሠባራ ጎን ነው።

  👉ተሻሻለ የተባለው በግልፅ አለመቀመጡ

በዚህ በኩል ዶ/ር ዘሩ በላይ ከተናገሩት ውጪ ለመናገር መሞከር የእሳቸውን ትልቅ ሃሳብ የማበላሸት ያህል ነው፤እሳቸው እንዳሉት ተሻሻለ የተባለው ካልተሻሻለው ተለይቶ መቀመጥ ነበረበት፤ኢንስትራክተር ሳሙኤል በምርጥ አቀራረብ ካቀረበው ውጪ የተሻሻለው የቱ እንደሆነ፣ያልተሻሻለው የትኛው ነው የሚለው በግልፅ ሲቀርብ አለመታየቱ ጥናቱን ጎዶሎ አድርጎት ወደ ውዝግብና ክርክር እንዲያመራ በር ከፍቷል።

👉ልምድና ትምህርት ይጣመሩ የሚለው አስታራቂ ሃሳብ

የውይይቱን ትኩሳቶች ከጨመሩት አጀንዳዎች አንዱ የአሠልጣኞች መምረጫ መስፈርት ትምህርት?ወይስ ልምድ? ይሁን የሚለው በዋናነት ይጠቀሳል፤ቤቱንም ለሁለት ከፍሎ ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዝ የነበረው ይኸው ብዙ መነቃነቅ የፈጥረው አጀንዳ ነው፤ትምህርት አስፈላጊነቱ ባይካድም ልምድና ውጤት ያላቸውን ግን መግፋት የለበትም የሚል የጠነከረ ተቋውሞ ቀርቧል።በዚህ በኩል አሠልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ”አንድ ሠው ትምህርት ካለው ካልተማረው በልጦ አሰርቶ የማይመጣው ለምንድነው?ተምረናል ያሉ ሠዎች ግን ከእኔ በላይ አስመርጠው፣ውጤትም አምጥተው አያውቁም፤የተማርከውን በተግባር ካላሳየህ የተማርከው ምንድነው?”የሚል መከራከሪያ ቀርቧል፤የአሠልጣኝ ህሉፍን መዘዝነው እንጂ

ውጤታማ የሆኑት የአሠልጣኝ ሀጂ አዴሎና የአሠልጣኝ ገመዶ ደደፎም ስጋት የህሉፍን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፤ልዩነቱን ለማጥበብና አቻችሎ ለመሄድ አሁንም በትምህርት ብዙ ርቀት የሄዱትን ግን ልምድና ውጤት ያላቸው አይገፉ የሚለውን የዶ/ር ዘሩ በላይንና የአሠልጣኝ ንጉሴ ጌቻሞን ገዥ ሃሳብ መውሠድ አዋጪ ነው፤አትሌቲክሱ ትምህርትንም፣ልምድና ውጤትንም አጣምሮ የሚሄድበትን መንገድ ጥናቱ ታሳቢ ቢያደርገው።

👉 ትልቁን ፌዴሬሽን የማይመጥነው”አዳራሹን ለቃችሁ ውጡ አለበለዚያ የመብራት አጠፋለሁ ዛቻ

“በዕውነት ይሄን ማየትና መስማት በጣም ያማል፤አለምን ጉድ ያስባሉ ታላላቅ አትሌቶችን ያቀፈውና በታላላቅ አትሌቶች የሚመራው ፌዴሬሽን ሠዓታችሁን ጨርሳችኃል አዳራሹን ለቃችሁ ውጡ አለበለዚያ መብራት አጠፋባችኃለሁ”የሚል ትንሽ ሠው ሲፎክርበትና “ጨርሠናል እባክህ ትንሽ ታገሠን አምስት ደቂቃ ብቻ”የሚል የፌዴሬሽኑን ሠዎች ልመናና ምልጃን ማየትና መስማት ምቾት አይሠጥም፤ፌዴሬሽኑንም የተሰብሳቢውንም ክብር ማሳነስ ነው፤የፈረጠመ የፋይናንስ ጡንቻ ያለው ፌዴሬሽን ለወጪ ቁጠባ ወይም የፀደቀ በጀት እጥረት አለብኝ ብሎ እዚህ ውስጥ መግባት የሚመከር አይሆንም፤ክብሩንም አይመጥንምና ይታሠብበት፤የሚለው የወፍ በረር ትዝብቴ መደምደሚያ ነው፤

በኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን የሚመራው ፌዴሬሽን በድፍረት ይሄን ሃሳብ ወደ መድረክ በማምጣቱ፣በአሠልጣኝነት መስፈርትና ደረጃ ዙሪያ አይነኬ የተባለውን ጉዳይ ደፍሮ ወደጉዳዩ ባለቤቶች በማምጣቱ ሁላችን “አበጃችሁ”በማለት ከፍ አድርገን ልናመሠግናቸው ይገባል፤

የፌዴሬሽኑ አመራሮች የተነሱትን ሃሳቦች በበጎ ጎን በመውሠድና በቀረበው ማስተካከያ መሠረት በማሻሻል ሁሉንም የሚያስማማ መስፈርት እንዲፀድቅ መትጋትም ይኖርበታል።

በቀጣይ በሚኖረኝ ዘገባ በውይይቱ ወቅት ውሃ የሚቋጥር አስተያየት የሠጡ ሠዎችን ሃሳብ በየተራ ለማቅረብ እንሞክራለሁ።
✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ (ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የክሪፕቶ ሥራ ፈጣሪው የ15 ዓመት እስር ተፈረደበት

የቀድሞው የክሪፕቶከረንሲ ሥራ ፈጣሪ ተሰውሯል ከተባለ 40 ቢሊየን ዶላር...

5ኛው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ...

የንግድ ሚኒስቴር 13 ምርቶችን በመነሻ ሀገር የጥራት ማረጋገጫ (PVoC) እንዲያገኙ ወሰነ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በሀገር...

ገዳ ባንክ ከ444 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በ2018 ዓ.ም...