እናቶች ምንም አይነት ፈተና ቢገጥማቸው የማይቻለውን በመቻል፣ ማንም ሊከፍለው የማይችለውን መስዋዕትነት በመክፈል ልጆቻቸውን በጽናት የማሳደግን ታላቅ ኃላፊነት በጀግንነት እየተወጡ ይገኛሉ።
በህንድ አንዲት ጀግና አውሮፕላን አብራሪ እናት በልጇ ሕይወት ላይ ያሳደረችው ተጽዕኖ ከሀገሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኗል።
ይህች አውሮፕላን አብራሪ እናት ከዓመታት በፊት የ5 ዓመት ሴት ልጇን በሄሊኮፕተር አብራ በረራ ታደርጋለች።
ይህች ታዳጊ የአብራሪዎችን ዩኒፎርም ለብሳ ከእናቷ ጎን በሄሊኮፕተር ለመጀመሪያ ጊዜ ከበረረችበት ጊዜ ጀምሮ የእናቷን ፈለግ በመከተል አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ህልም አላት።
ከጥቂት ዓመታት በኋላም በዴልሂ አየር ማረፊያ አብራሪዎች ዩኒፎርም ለብሰው የጉዞ ሻንጣቸውን ይዘው ሲንቀሳቀሱ እና በአየር ማረፊያው የነበረው ሰው ሁሉ በአክብሮት ሲመለከታቸው ማየቷ አብራሪ የመሆን ሕልሟን የበለጠ አጠናከረላት።
ይህች ወጣት የተሰጧትን አምስት የተለያዩ ፈተናዎች በሙሉ በመጀመሪያው ዙር በማለፏ በ18 ዓመቷ የንግድ አውሮፕላን አብራሪነት ፈቃድ ተሰጥቷታል።
አውሮፕላን አብራሪዋ እናት በሴት ልጇ ልብ ውስጥ የዘራችውና ያበቀለችው ህልም እውን ሆኖ ይህች ወጣት በ18 ዓመቷ በሀገሪቱ ታሪክ በታናሽ የንግድ አውሮፕላን አብራሪነት ተመዝግባለች።
ምስጋና ለእናትየው ይሁንና ፓይለት ሰሚራ ሁለር በአሁኑ ጊዜ በህንድ የንግድ አውሮፕላን አብራሪ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።
ይህች ወጣት የአብራሪነት ፈቃዱን ካገኘች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሌሊት ያለምንም ችግር ለ200 ሰዓታት መብረር እንደቻለችም ተገልጿል።
