ኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ሊደግፍ የሚችለውን የአፍሪካ ስታርት አፕ ኢኮ-ሲስተም ጉባኤና አዋርድ ለመጀመሪያ ጊዜ አካሂዳለች።
ጉባኤውና አዋርዱ ከቅዳሜ ሕዳር 6 እስከ ዛሬ ሕዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ተከናውኗል።
ይህ የጉባኤና አዋርድ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ በዚህ መረሃ ግብር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የሥራ ፈጣሪ ተቋማት እና ልዩ ስጦታ ያላቸው ወጣቶች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ለሽልማቱ እጩ ለመሆን የተመረጡት ተቋማትና ወጣቶች የሚያሟሉት መስፈርትም፤ በቴክኖሎጂ፣ በአይሲቲና ግብርናው ዘርፍ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል።
የጉባኤው ዋናኛ አላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፖሊሲ አውጭዎችን፣ ባለሃብቶች፣ አማካሪዎችንና ሥራ ፈጣሪዎችን በፋይናስና በእውቀት መደገፍ መሆኑን ተጠቁሟል።
ከጉባኤው አዘጋጆች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ቃልኪዳን ሻሹግ እንዳስታወቁት ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቷ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎቿ ከሌሎች የአፍሪካ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ጋር ተገናኝተው ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመለዋወጥ እንዲያሳድጉ ትልቅ ፋይዳ አለው።
ሌላኛው የጉባኤውና የአዋርዱ አዘጋጅ የሆነው የሪች ፎር ኢትዮጵያ የፕሮግራም ባለሙያ ኤልሳቤት ፀጋዬ በመረሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ከኢትዮጵያ ጨምሮ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬኒያና ከኡጋንዳ የተውጣጡ የሥራ ፈጣሪ ተቋማትና ወጣቶች እንደሆኑ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህ በመሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ሥራ ፈጣሪ ተቋማትና ወጣቶች በዘርፉ ላይ የዳበረ ልምድና እውቀት ካላቸው ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ልምድ በመቅሰም በጋራ ለማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ስታርት አፕ ኢኮ ሲስተም ጉባኤ እና አዋርድ በእ.ኤ.አ በ2022 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ በአፍሪካ ውስጥ ባሉ የስነ-ምህዳር ገንቢዎች ዘንድ ግንባር ቀደም መድረክ ሆኗል።
እስከአሁን ድረስም ከ44 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ8 ሺሕ 500 በላይ የስነ-ምህዳር ገንቢዎች ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የተሳተፉ ሲሆን፤ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ጀማሪ ኩባንያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ባለሀብቶችን በመድረኩ ተካፍለዋል።
ኢትዮጵያም የዘንድሮውን አራተኛ የአፍሪካ ስታርት አፕ ኢኮ-ሲስተም ጉባኤንና አዋርድ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዘጋጀት ዕድል አግኝታለች።
አሐዱ ራዲዮ
