የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገዉን የሁለት ቀናት ጉባኤ ትናንት አጠናቀቀ።
አንጋፋዉ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ ኦነግ በርካታ አባላቱና ባለሥልጣናቱ በመታሠራቸዉና ጉለሌ-አዲስ አበባ የሚገኘዉ ዋና ፅሕፈት ቤቱ በመዘጋቱ ለአምስት ዓመታት ያክል የማዕከላዊ ኮሚቴ ሥብሰባ አድርጎ አያዉቅም።
የኦነግ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ እንዳሉት ፓርቲያቸዉ ባለፉት አምስት ዓመታት ያለቢሮ መንቀሳቀስን ጫምሮ «በርካታ ተግዳሮቶችን አሳልፏል”።
በቅርቡ ግን አብዛኞቹ ባለሥልጣናቱ በመፈታታቸዉና ፅሕፈት ቤቱም በመከፈቱ ግንባሩ የወትሮ ሥራዉን ለመከወን መንቀሳቀስ ጀምሯል።
የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴም ለሁለት ቀናት ያደረጉዉን ሥብሰባ ትንናንት ሲያጠናቅቅ ባወጣዉ መግለጫ «የተፈጠሩትን ድርጅታዊ ክፍተቶች ለመድፈን» በአጭር ጊዜ ውስጥ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ አዘጋጅ ኮሚቴ ማዋቀሩን ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ ኃይላት ጋር የገጠመዉን ዉጊያ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኦነግ ጠይቋል፡፡
