ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 64 ተማሪዎች ለማስመረቅ አዲስ አበባ የተገኙት የዩኒሳ ሀላፊዎች ከትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር የትምህርት አድማሱን ለማስፋት በሚቻልበት መላ ላይ ከሰሞኑ ወይይት ማድረጋቸውን ከዩኒቨርሲቲው ሰምተናል።
UNISA ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ከ2006 ጀምሮ በትምህርት፣ በምርምር እና በቴክኖሎጂ መስክ በርካታ ተማሪዎችንና የመንግስት ሰራተኞችን ሲያስመርቅ መቆየቱን የዩኒሳ ምክትል ቻንስለር ለሚኒስትሩ አብራርተውላቸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ ለያዘቻቸው የልማት እቅዶች መሳካት የሚያስፈልግ የሰው ሃይል ልማትን በሚያግዙ የትምህርት መስኮች እንደ ማዕድን፣ ፔትሮ ኬሚካል፣ አግሮ ኢንደስትሪ የመሳሰሉት ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆን ይገባቸዋልም ማለታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ሰምተናል።
ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየትኞቹ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት እንደሚቻል እንዲለዩና ለቀጣይ ውይይት መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮች እንዲያቀርቡ ተስማምተዋል ተብሏል።
በአለም ዙሪያ ተማሪዎች ያሉት ዩኒሳ ሙሉ ለሙሉ የርቀትና የኦንላይን ዩኒቨርሲቲ ሲሆን የትምህርት ማዕከል ያለው በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር መሠረት መለሰ ነግረውናል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ የተከፈተውም በርቀትና በኦንላይን የሚሰጠውን ትምህርት ለማቀናጀት መሆኑንም ሰምተናል።
ከደቡብ አፍሪካ ውጫ ብቸኛው የዩኒሳ ማዕከል የሆነው የኢትዮጵያ ሪጅናል የትምህርት ማዕከል፣ ለኢትዮጵያውያን የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ከመግቢያ ጀምሮ እስከ ምርቃት ድረስ አጠቃላይ የአካዳሚክ እና የአስተዳደራዊ ድጋፍ ይሰጣል።
ማዕከሉ ለተማሪዎች ምዝገባ ከማገዝ ጀምሮ የወርክሾፕ፣ ቤተመጻሕፍት፣ ኮምፒዩተር የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ይሰጣል፤ ትምህርት የሚሰጠው ግን ሙሉ ለሙሉ ከደቡብ አፍሪካ መሆኑን አቶ መሠረት መለሰ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ማዕከል ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ 629 የዶክትሬት እና 382 የማስተርስ ተመራቂዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 1,163 ተማሪዎችን አስመርቋል ተብሏል።
አብዛኞቹ ተመራቂዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊነት፣ የንግድ ድርጅቶች እና በሌሎች ዘርፎች በሀላፊነት እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል።
#UNISA በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መንግስት ትብብር አማካይነት በኢትዮጵያ ማዕከል ከተከፈተ 18 ዓመት እንደሆነው ሰምተናል።
ዩኒቨርስቲው በትናንትናው እለት 58 በፒኤችዲ እና 6 የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ስነ-ስርዓቱ ላይ የዩኒሳ ፕሪንሲፓል እና ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ፑሌንግ ሌንካቡላ ተገኝቸዋል።
ሸገር 102.1
