ከየካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በሚፈጸሙ ማንኛውም የባንክ ግብይቶች ላይ አዲስ የአገልግሎት ክፍያ ስሌት ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ለሁሉም ባንኮች ባስተላለፈው ጥብቅ ማሳሰቢያ መሠረት፣ በደንብ ቁጥር 576/2018 ዓ.ም. ላይ በተቀመጠው የማስከፈያ ስሌት መሠረት ክፍያዎችን በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለተከፈተው “የኢትዮጵያ አደጋ ስጋትና ምላሽ ፈንድ” ፅህፈት ቤት ሂሳብ ገቢ እንዲያደርጉ ታዘዋል።
በዚህም መሠረት በዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች ከሚከፍሉት መደበኛ የአገልግሎት ክፍያ ላይ የ5% (አምስት በመቶ) ተጨማሪ ክፍያ የሚሰበሰብ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ባንኮችና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት ማንኛውም ዓይነት መደበኛ ብድር ላይ የ1% (አንድ በመቶ) የፈንድ ክፍያ ተጨምሮ የሚሰበሰብ መሆኑ ካፒታል ጋዜጣ ከፋይናንስ ተቋማቱ ያገኘዉ መረጃ ያመለክታል።
እንደ አዲሱ መመሪያ ዝርዝር ሁኔታ፣ ይህ የገቢ አሰባሰብ ሌሎች ዘርፎችንም የሚጨምር ሲሆን፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች የፕሪሚየም ክፍያ ላይ 1%፣ ከአገር ውስጥ አየር በረራ የቲኬት ሽያጭ ላይ 100 ብር፣ ከቴሌኮሙኒኬሽን ድምፅና ዳታ አገልግሎት የአየር ሰዓት ሽያጭ ላይ 5%፣ እንዲሁም ከነዳጅ ሽያጭ በእያንዳንዱ ሊትር ላይ 1 ብር ለፈንዱ ገቢ ይደረጋል።
ይህ አዲስ አሰራር የአገሪቱን የአደጋ ስጋት የመከላከልና ምላሽ የመስጠት አቅም ለማጠናከር ታስቦ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል። በየካቲት ወር የሚሰበሰበው ክፍያም እስከ መጋቢት ወር ድረስ ለፈንዱ ገቢ እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል።
