ልክ እንደተፈጥሮ ጋዝ ሁሉ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት እንዳለ በሶስተኛ ወገን መረጋገጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ነዳጅ ማጣሪያውንም በ24 ወራት ውስጥ አጠናቅቀን እንጨርሳለን ብለዋል።
የጋዝና ነዳጅ ሥራ ከውጭ የሚገባውን ኃይል በመተካት የወጪ ምንዛሬ ለመቆጠብ ይረዳናል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለነዳጅና ለማዳበሪያ ከፍተኛ ሃብት ታወጣለች፤ ይህን ማስቀረት ከቻልን ብዙ ሃብት ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሰዎች ጋዝና ነዳጅ እናልማ ወይም ወርቅ እናውጣ ብለው ፈቃድ ይወስዱ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካቶች ፈቃድ ወስደው የሚያሰራቸውን ሰው እየፈለጉ እንደሚቆዩና ሥራው እንደማይሰራ አመላክተዋል።
አብዛኛው ፈቃድ ወሳጅ አልሚ ሳይሆን ደላላ መሆኑን አስታውሰዋል፤ ይህ ችግር በጋዝ ብቻ ሳይሆን በወርቅም እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ይህን ችግር በመፍታት ውጤታማ ለመሆን መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉንም አብራርተዋል።
