‹‹ከኢሳያስ ወግነው አብይን ማስወገድ የሚፈልጉ አሉ›› ጀነራል ፃድቃን
ጄነራል ጻድቃነው ገብረ ትንሳይ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል “በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡ በትግራይ አመራሮች መካከል ያለውን ክፍፍል በመጥቀስ “ከቀደመና ከአሁንም ወንጀላቸው ተጠያቂነት ለማምለጥ ከኤርትራ ጋር መወገን የሚመርጡ የትግራይ ልጆች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ መሰማት የተጀመረው ጄኔራል ፃድቃንም ይህንን የህወሓት ክፍፍል በመጥቀስ “ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመወገን ዐቢይ አሕመድን ከሥልጣን ለመገልበጥ” የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
“በጦርነቱ ማዕከላዊ የምትሆነው በደንብ የሠለጠነና ልምድ ያካበተ ከፍተኛ የወታደር ቁጥር ያላት ትግራይ ናት” ሲሉም አክለዋል።
ጄኔራል ፃድቃን “ትግራይ ከዚህ ጦርነት መራቅ” እና “ሰላም እንዲሰፍን” እንደምትሻ በጽሑፋቸው ገልጸዋል።
“ለሰላም ያለው ዕድል እየጠበበ ቢሆንም ወደ ግጭት ላለመግባት ሁሉንም መንገዶች መጠቀም እንደሚያሻ” ተናግረዋል።
ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠልሸቱን በማስታወስ ጦርነት “አይቀሬ” መሆኑንም ጄኔራሉ ጠቅሰዋል።
“ዝግጅቱ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው። ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት አንዳች ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደኋላ መመለስ ይከብዳል” ብለዋል።
እየመጣ ባለው ጦርነት ምክንያት ትግራይ ከአካባቢያዊ ፖለቲካ፣ታሪክና ባህልም አንጻር ስጋት ውስጥ እንደሆነች የተናገሩት ጄኔራል ፃድቃን “የኔ ምርጫ ትግራይ ለሰላም ጥሪ እንድታደርግ ነው። ብዙ ተሰቃይተናል” ብለዋል።
ሆኖም ግን “መሪዎች ከድርድር ይልቅ ጦርነትን በሚመርጡበት ወቅት” በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለሚኖረው ጦርነት የጦር አውድማ ትግራይ እንደምትሆን ስጋታቸውን በጽሑፋቸው አስተጋብተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳም “በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በግልጽ የሚታይ መቃቃር አለ። የእኔ ስጋት ይህ ከቃላት አልፎ ወደ ጦርነት እንዳያድግ ነው” ብለዋል።
ቢቢሲ
