በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስደት የተለመደውን ትምህርት ላይ መሰረት ያደረገ የህይወት መንገድ በመተካት ላይ ይገኛል።
ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በሁሉም የትምህርት ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት ቢስፋፋም አብዛኞቹ ተመራቂዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ስራ ለማግኘት ይፈተናሉ።
70 በመቶ ህዝቧ ከ30 አመት በታች በሆነችው ኢትዮጵያ የከተማ የወጣቶች የስራ አጥነት ምጣኔ በ2022 25.3 በመቶ ነበር።
ከኢትዮጵያ በየአመቱ ታዲያ ከ250,000 በላይ ሰወች ከሃገር ይሰደዳሉ ሲባል መደበኛ ያልሆነ ስደትም የብዙሃንን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል።
ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያደርጉ ምክንያቶች
ከ2000ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ወጣቶች በህጋዊ መንገድ ወደ ባህረ ሰላጤው ሃገራት መጓዝ ሲችሉ የአብዛኞቹ መዳረሻም ሳዑዲ አረቢያ ነበረች።
ከ2013-2018 ኢትዮጵያ በነዚህ ሃገራት የሚሰሩ ዜጎች እየሞቱ መሆኑን ተከትሎ በጊዜያዊነት ሰዎች ለስራ ወደነዚህ ሃገራት እንዳያመሩ እገዳ አስቀምጣ ነበር። በነዚህ ጊዜያትም በርካታ ሰዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሃገር ይወጡ ነበር።
በቂ የስራ ዕድል አለማግኘት፣ ግጭቶች እና አለመረጋጋት፣ በውጪ ሄዶ የተሻለ ኑሮን ለመኖር መመኘት፣ ቢዝነስ የመጀመር መንገዶች ውስንነት ሰዎች ስደትን የሚመርጡባቸው ምክንያቶች ናቸው።
በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ስደት እንደ አጭርና ምርጡ የገቢ ማግኛ መንገድ ተደርጎ ሲወሰድ ውጪ ሃገር ዘመድ ያለው ሰውም ይከበራል የሚል ባህል አለ።
ሌላኛው ምክንያት በአማራ፣ ኦሮሚያ እንደዚሁም ትግራይ ክልል ያሉና የነበሩ ግጭቶች ወጣቶች መረጋጋትን ለማግኘት ስደትን እንዲመርጡ ሲገፋፋ ወጣቶቹ በጦርነት ወቅት ያላቸው ምርጫ ማቆሚያ አልባውን ጦርነት መቀላቀል አሊያም መሰደድ ነው።
በተጨማሪነት የሚነሳው ሌላኛው ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት በህጋዊ መንገድ ለመውጣት የሚያስፈልጉ ህጎችን ጠንካራ ማድረጉ ነው።
ለምሳሌ እንደ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የትምህርት ደረጃ ወዘተ ያሉ ነገሮች ከሃገር መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች በቀላሉ ሊያሟላቸው የሚችሏቸው ነገሮቸ አይደሉም።
ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች በራሱ አብዛኛው በቀላሉ ሊያሳካው የሚችለው ጉዳይ ስላልሆነ በህገወጥ መንገድ መሰደድን እንዲመርጡ ያደርጋል።
ሌላኛው ጉዳይ በህጋዊ መንገድ መሄድ ቢፈልጉ ጥቂት ዕድሎችን ብቻ ማግኘታቸው ነው። ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር የተፈራረመቻቸው ስምምነቶች የስራ ዕድልን የሚያቀርቡት በብዛት ሴቶች የሚሳተፉባቸው ለቤት ውስጥ ስራ መሆኑ የወንዶቹን እና የቤት ውስጥ ስራዎችን መስራት ለማይፈልጉት ምርጫቸውን ይገድባል።
የስደት መንገዶች
የመጀመሪያው በምስራቅ ያለው ሲሆን ይህም የቀይ ባህርን በመሻገር በየመን አድርጎ ሳዑዲ አረቢያ መግባት ነው።
ከ2014 ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ76 ሺህ በላይ ስደተኞች ሲሞቱ 1098 ያህሉ የሞቱት በዚህ መንገድ ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ በባህር ውስጥ ሰጥመው ነው።
በ2021 የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት እንዳስታወቀው ከተጠቀሰው አመት በፊት በነበሩ 5 አመታት ከሃገር የወጡ 51 ሺህ ኢትዮጵያውያን የገቡበት አልታወቀም።
ሁለተኛው ደግሞ የደቡብ መንገድ ሲሆን ይህም ከደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ ናቸው
ይህ መንገድ ሁለተኛው ትልቁ የህገወጥ የስደት መንገድ ሲሆን ሶስተኛው መንገድ በሱዳን፣ ሊቢያ እና ሜድትራንያን ባህር አድርገው አውሮፓ የሚገቡ ናቸው።
ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ?
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የኢኮኖሚ ዕድሎችን መፍጠር ሲጠበቅባት መንግሰትም የሙያ እና የስራ ፈጠራወችን በገጠራማው አካባቢ መደገፍ ይኖርበታል።
ሁለተኛው ህጋዊ የመሄጃ መንገዶች ማስፋፋት ነው። ይህም ከተለያዩ ሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማድረግ ሊጠናከር ይገባል። እነዚህ ስምምቶቸ ሲደረጉ ወጣቶች ሊሰሩባቸው የሚችሉ የስራ ዘርፎችን ማካተትም ይገባል።
ህጋዊ ከሃገር የመውጫ መንገዶችንም ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንዲወስኑ ትምህርቶችን መስጠትም ያስፈልጋል።
በተጨማሪ ሙያን መሰረት ያደረጉ ትምህርቶች እና የስራ ዕድሎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል።
[ የዚህ ጹሑፍ ዋናው ቅጂ በThe Conversation ላይ ማግኘት የሚቻል ሲሆን ጹሑፉ የዶ/ር ግርማቸው አዱኛ ነው። ]
@TikvahethMagazine
