በቅርበት ከማውቃቸውና ልዩ ከምላቸው ሰዎች ውስጥ ነበረች። ድንገት በታወቀ የካንሰር ህመም፤ አደጋ በሚመስል ፍጥነት ተለየችን። የሚያውቃት ሁሉ ምነው ባላወኳት ሲል ልቡ ተሰበረ። እኔ ግን እላለሁ እንኳንም አወኳት። እንኳንም እህቴ ሆነች።
በዚህ ዘመን እንደመልዓክ በዙሪያችን ተከስተው፤ ፈገግ እንዳሉ ብርሃናቸውንና ፍቅራቸውን ነስንሰው፤ ድንገት እንደመጡት ድንገት የሚሄዱ ጥቂት ሰዎች አሉ። እነሱን ማግኘት መታደል ነው። መባረክም ነው። ልባችንን በፍቅር ሞልተው፤ አይምሯችንን በመልካም ሃሳብ ወልውለው፤ ወደውን አፅድተውን የሚሄዱ ጥቂት ናቸው።
ግን እንኳንም አወቅናቸው።
እግዚዓብሄር ሆይ!
እንዲህ አይነቶቹን ቶሎ ትፈልጋቸው ሳለ ግን ደግሞ ስለሰጠኸን እናመሰግንሃለን እንበለው እንጂ አናማረው። የሰጠንም እሱ ነውና!
ህመሟን ልትነግረኝ ደወለችልኝ… እንዴት ነሽ ቡቡዬ? አልኳት።
እግዚዓብሄር ይመስገን! አለችኝና ስራ ይዘሃል? አለችኝ።
ሁልግዜ ነፃ መሆኔን አረጋግጣ ነው ወሬ የምንጀምረው… በቀደም ሳምፕል የተላከው ውጤት መጣ ስትለኝ ፈገግታም ደስታም ያለበት ድምፅ ስለነበር… ውይ ጎሽ ብዬ ውጤቱ ጥሩ ሆነ አይደል? አልኳት…
አዎ ምንም አይልም ያው የሚያሳይ ነገር አለ። አለችኝ
ምን? ስላት… መደንገጥ የለም! በጣም ደህና ነኝ ። ግን እንዲህ እንዲህ ነው… ብላ በሽታውን ቀለል አርጋ ፈገግ እንዳለች እንደቀልድ ነገረችኝ!
ለቀልድም ስለማትዋሽ እኔ ስብርብር አልኩና የሷን ጥንካሬ እንዳልሰብር ብዬ አንዴ ስልክ ልመልስ ብዬ ዘወር ብዬ እራሴን አረጋግቼ ተመለስኩ!
ይህን ነገር የምታውቁት አንተና እልፌ ብቻ ናችሁ ብላ የምትወዳት ጓደኛዋ እልፍነሽ እንደምታውቅ ነገረችኝ። በጣም የምትወዳቸው ሁለት ወንድሞችና አምስት እህቶች አሏት። ከራሷ በላይ የምትወደው ባልና ከአይን የማትለያቸው ሁለት ልጆች አሏት። ታዲያ ይህንን ለኔ የነገረችኝ ጠንካራ ነህ ብላ አይደል?! ለመጠንከር ሞከርኩ። ግን እሷ እንዳሰበችኝ ጠንካራ አማኝ እንዳልሆንኩ ገባኝ።
ያኔ… የኔን እምነት ከሷ እምነት ጋር ለካሁትና ለራሴ አዘንኩ።
ቡቡዬ…. አይዞህ አልሞትም እንዳልሽው አዎ አትሞቺም። መልካም ሰው ነበርሽ ደግሞም ፍፁም ወደ ሆነው አባትሽ ሄድሽ እንጂ አልሞትሽም።
የታመምኩት ለበጎ ነው። የተኮራረፈ እንዲታረቅልኝ፤ የተጠፋፋው እንዲገናኝልኝ ነው አልሽ….
ማነው በስቃይ ውስጥ ሆኖ ሞትን አርግዞ ይህንን የሚያስብ? መልዓክ ካልሆነ በስተቀር!
አይዟችሁ! ለበጎ ነው! ፈገግ በሉ! አላመመኝም! ቀላል ነውኮ!….
የምትያቸው ቃላቶችሽ ጆሮዬ ላይ ናቸው። ፈገግ እንዳልሽ እዝች አለም ላይ ስንመጣ እንጂ ስንሄድ ልናለቅስ እንደማይገባን አስተምረሽናል። ከሺህ ቃላት ይልቅ ያንቺ ተግባር ያነቃል።
ሰው በዚህ ልክ እምነት አለው?!
ሰው በዚህ ልክ መልካሙን ብቻ ያስባል?!
ያንቺስ የተለየ ነው።
ለክፉ ሰው እንጂ ለደግ አይለቀስ እል ነበር። ብችል ባላለቀስኩ! ግን አቃተኝ!
ያንቺ ጥንካሬ፣ ያንች እምነት የለኝም!
ለባለቤቷ ለሃይሉ ተክለስላሴ (ዶ/ር)፤ ለልጆቿ ለጄሪዬና ለናቲ፤ ለወንድሞቿና ለእህቶቿ፤ ለጓደኞቿና በልጅነቷ በኢትዮጵያና አሁንም በአሜሪካን ቨርጂኒያ ግዛት ስትኖር ለምታውቋት ለምትቀርቧት ሁሉ ከዚህ ከባድ ሃዘን እግዚዓብሄር እንዲያፅናናችሁ ምኞቴ ነው።
አብርሃም ወልዴ
