በአዲስ አበባ በሚገኘው ሚሊኒየም አዳራሽ ከግንቦት 7 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሊካሄድ የነበረው “ሜድ ኢን ፓኪስታን” ኤግዚቢሽን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ተሰምቷል።
ይህ የንግድ ትርኢት ከ100 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ የፓኪስታን አምራቾችን በማሳተፍ በጨርቃ ጨርቅ፣ በመድሃኒት፣ በኢንጂነሪንግ፣ እና በግብርና ምርቶች ማቀነባበርን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የኤክስፖርት አቅም እና የፈጠራ ምርቶቻቸውን ለማሳየት ታቅዶ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የዝግጅቱ አዘጋጆች ባወጡት መግለጫ በቅርቡ በህንድ እና በፓኪስታን መካከል በተፈጠረው አስገዳጅ ሁኔታ ማለትም ግጭት ምክንያት ኤግዚቢሽኑ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን አሳውቀዋል።
ይህ የሶስት ቀናት ዝግጅት በፓኪስታን መንግስት በንግድ ሚኒስቴር፣ በፓኪስታን የንግድ ልማት ባለስልጣን (TDAP) እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የፓኪስታን ኤምባሲ የንግድ ክፍል የተዘጋጀ ሲሆን የንግድ-ለ-ንግድ (B2B) ግንኙነቶችን ለማጠናከር እና ጠቃሚ ሽርክናዎችን ለመፍጠር ምቹ መድረክ ለመፍጠር ታቅዶ ነበር።
አዘጋጆቹ ይህንን በቀጣይ ስለ ዝግጅቱ የሚኖር ሂደት በደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት የሚገለጽ መሆኑንም አሳውቀዋል።
CapitalNews
