በ2017 በጀት ዓመት በ10 ወራት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ኤክስፖርት አፈጻጸም ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳህለ ማርያም ገብረ መድህን ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት በዚህ ጊዜ ውስጥ ከቡና ሽያጭ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡
አያይዘውም በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ከ354 ቶን በላይ ቡናን ለውጪ ገበያ በመላክ ይህ ገቢ ተገኝቷል ሲሉ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።በዚህም ከእቅድ በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀው አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ70 በመቶ እንዲሁም በገቢ የ869 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
ይህ አፈፃፀም በኢትዮጵያ የአንድ አመት ኤክስፖርት ታሪክ እንኳ ተገኝቶ የማያውቅ እና የመጀመሪያ የሆነ ኤክስፖርት አፈጻጸም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት አሥር ወራት የተላከዉ ቡና በመዳረሻ ሀገራት ሲታይ ጀርመን ቀዳሚውን ድርሻ ስትይዝ ሳዉድ አረቢያ እና አሜሪካ የ2ኛና የ3ኛ ደረጃን መያዛቸውንም አቶ ሳህለ ማርያም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ የላቀ አፈጻጸም የመንግስት፣ የአርሶአደሩ ፣የአቅራቢው፣ የአልሚው፣ የላኪው እንዲሁም ክልሎችን ጨምሮ የመላው ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት አስተዋፅኦ ማድረጉን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
