የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ (ኦፌኮ) በ2018 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ አስቻይ ሁኔታ ከሌለ እንደማይሳተፍ አስታውቋል።
ፓርቲው ይህን ውሳኔ ካደረገ ለሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ራሱን ያገለለ ይሆናል።
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ በምርጫው ለመሳተፍ እና የቅስቀሳ ስራዎችን በነጻነት ለመስራት ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ፓርቲው በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ለማሟላት አይንቀሳቀስም።
ኦፌኮ ከዚህ በፊት በ2014 ተካሂዶ በነበረው ሀገራዊ ምርጫም አልተሳተፈም።
በቀጣይ በሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም የማይሳተፍ ከሆነ፣ በምርጫ እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት ህጋዊ እውቅናው ሊሰረዝ ይችላል።
አቶ ሙላቱ “ብንሰረዝም እንሰረዝ እንጂ አስቻይ ሁኔታ ከሌለ መስፈርት ለማሟላት ኦፌኮ በምርጫው አይሳተፍም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል፣ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ቀደም ሲል ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረው ነበር።
አንዳንድ ሰላም የሌላቸው አካባቢዎችም ምርጫው እስከሚደርስ ድረስ ሰላም ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል።
